መቅድም
Derib Ado, PhD Editor-in-chief of JECS
Abstract
በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል ሥር የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት ቅጽ ፱ በጸሓፊዎች እና አርታዒዎች ያላሰለሰ ጥረት እነሆ ለኅትመት በቅቷል፡፡ ሁላችንንም እንኳን ደስ አለን፡፡ ይህ ቅጽ እንደቀደምቶቹ ቅጾች በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የቀረቡ በአጠቃላይ ስድስት ጽሑፎችን የያዘ ነው። ሦስቱ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ ሲሆኑ፣ ሦስቱ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የቀረቡ ናቸው፡፡ ጽሑፎቹ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሕይወት፣ በተማሪዎች መንፈሳዊ ትምህርት ተመክሮ እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥና በሃይማኖቶች መካከል ያሉ ግጭቶችን በመተንተን ላይ ያተኮሩ ናቸው። የመጀመሪያው ጽሑፍ በ፲፰ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተወልደው፣ በ፲፱ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩትን የአለቃ ምላት ምሕረትን የሕይወት ታሪክ የሚያትት ሲሆን፣ በጽሑፉ ስለትውልዳቸው፣ ስለአስተዳደጋቸው፣ ስለተማሩባቸው እና ስለአገለገሉባቸው አድባራት፣ በሕይወታቸው ስለገጠማቸው ፈተና ያትታል፡፡ ጽሑፉ የአለቃ ምላትን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና መንፈሳዊ ሕይወት የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ ሰውየው በቤተ መንግሥቱም በኩል የንጉሥ አማካሪ እስከመሆን የደረሱበትን ጉዞ በአብነት በማንሳት የቀደሙ አባቶች የነበራቸውን ዘርፈ ብዙ ሚናና አገልግሎት በእሳቸው ሕይወት አማካኝነት አቅርቧል፡፡ ሁለተኛው ጽሑፍ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተሳታፊ ስለሆኑ የቆሎ ተማሪዎች የሚያትት ነው፡፡ ጽሑፉ በግል ተሞክሮ፣ በመስክ ምልከታ እና በቃለ መጠይቅ የተገኘን መረጃ ዋቢ በማድረግ በተለምዶ የቆሎ ተማሪዎች ስለሚባሉ የአብነት ተማሪዎች ልዩ የትምህርት ጉዞ የሥነ ባህል ጥናትን መሠረት በማድረግ በሰፊው ትንተና ሰጥቷል፡፡ ከተነሡት ዋና ዋና ጉዳዩች መካከል ተማሪዎቹ ምግባቸውን ለምን እና እንዴት ለምነው እንደሚበሉ፣ የትምህርት አሰጣጡ ምን እንደሚመስል እንዲሁም በተማሪዎች መካከል ያለው መንፈሳዊና ማኅበረሰባዊ መስተጋብር ለመማር-ማስተማር ሂደቱ ምን አስተዋጽኦ እንዳለው በጥልቀት የተተነተነበት በአብነት ይጠቀሳሉ።