መቅድም
Abstract
ማኅበረ ቅዱሳን ይህን በብዙ ልፋትና ድካም ለኅትመት የበቃውን፣ ፰ኛውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት (ኢ.ቤ.ጥ.መ.) ለአንባብያን ሲያቀርብ በታላቅ ደስታ ነው፡፡ መጽሔቱ የቤተ ክርስቲያንን ልዩ ልዩ ገጽታዎች ሊያሳዩ የሚችሉ አምስት መጣጥፎችንና አንድ የመጽሐፍ ግምገማን ያካተተ ነው፡፡ ይህም በዘርፉ ያለውን መልከ ብዙ እውቀት በጨረፍታም ቢሆን ለማየት የሚያስችለንን ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ መጽሔቱ ስድስት የምርምር ውጤቶችን የያዘ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ሦስቱ በአማርኛ ቋንቋ የቀረቡ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ሦስት የምርምር ውጤቶች ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ከቀረቡት መካከል የመጀመሪያው መጣጥፍ፣ በኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ከጥንት ጀምሮ እየተተገበረ በኖረው፣ በብራና ጥበብ አሠራርና አዘገጃጀት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የእስቴ ወረዳን በማሳያነት የተጠቀመው ይህ ጥናት፣ የብራና ጥበብ አሠራርና አዘገጃጀትን የሚያቀርብ ብቻ ሳይሆን፣ የሙያውን ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ እንዲሁም ታሪካዊ ገጽታ የሚያሳይ ነው፡፡ ሁለተኛው መጣጥፍ፣ የፎክሎር ጥናት የቤተ ክርስቲያንን ገዳማትና ቅዱሳት ቦታዎች በማስተዋወቅ ረገድ የሚጫወተውን አዎንታዊና ገንቢ ሚና በማሳየት ላይ ያተኮረ ነው። ጥናቱ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ አተኩረው የተሠሩ ቀደምት የፎክሎር ጥናቶችን በመገምገም ባህላዊ ሁነቶችን፣ ንዋያተ ቅድሳትን፣ ገዳማትንና ቅዱሳት ቦታዎችን በጥልቀትና በስፋት ለመረዳት የፎክሎር ጥናቶች ጠቃሚ መሆናቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ያቀረበ ነው፡፡ በዚህ ቅጽ ሥር የተካተተው ሦስተኛው መጣጥፍ ደግሞ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸውን ሚኒራሎች ሳይንሳዊ በሆኑ ስሌቶችና ስልቶች ለመተንተን የቻለ ነው፡፡ እነዚህ ሚኒራሎች በዋናነት በቤተ መዘክርና ቤተ መዛግብት ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ በቤተ ክርስቲያኗ ባለቤትነት ሥር ያሉ ናቸው፡፡