Trinitarian Concept of Ecclesiology in the Writings of St. Yared: As Reflected in the Book of Dïgga
Muluneh Getie
Abstract
ነገረ ቤተ ክርስቲያን የቅርብ ጊዜ የትምህርተ እግዚአብሔር የትኩረት ዘርፍ እየሆነ የመጣ የጥናት ክፍል ሲሆን በቀደሙት ቅዱሳን ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያን አበው ዘንድ እንደ ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ በደንብ የተለካና የተቀነበበ ሥርዐተ ትምህርት አልተበጀለትም፡፡ ባለ ቅኔና የዜማ አባት የሆነው የ፮ኛው ክ/ዘመን የትምህርተ እግዚአብሔር ሊቅ የሆነው ቅዱስ ያሬድም የቅዱሳን አበውን የአስተምህሮ ዱካ በመከተል ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን በተናጠል አልጻፈም፡፡ ነገር ግን ኹሉን ዓቀፍ ይዘት ባላቸው ድርሳናቱ ውስጥ ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን በስፋት በማተት የሥላሴ መሠረት ስላላት ቤተ ክርስቲያን መነሻ መሠረትና የሕይወት ጉዞ በጥልቀት አመስጥሮ ጽፏል። ይሁን እንጂ ይህ ከቀደሙት ቅዱሳን አበው ምድብ የሆነው ቅዱስ ያሬድ የጻፈው የሥላሴ መሠረት ያለው ጥልቅ የነገረ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከነገረ እግዚአብሔር ሊቃውንት የጥናት ትኩረት ርቆ የቆየ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ ከቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች መካከል አንዱ በሆነው መጽሐፈ ድጓ ውስጥ ነገረ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተገለጸ ዐይነታዊ በሆነ የጥናት ስልት ማቅረብና መተንተን ነው፡፡ ጥናቱም የነገረ ቤተ ክርስቲያን መሠረትና ሕይወት ክርስቶስ ብቻ ወይም መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው ከሚለው ከካቶሊክና ፕሮቴስታንቲዝም አስተምህሮ በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሥላሴን የምትቀበል እንደሆነች የሚያሳይ ነው። ይህም ከቀደሙት አበው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አስተምህሮ ጋር አንድ ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ የቤተ ክርስቲያን ፅንሰ ሐሳብ በሥላሴ ተፈጥረው በኤዶም ገነት ይኖሩ ከነበሩት የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች፣አዳምና ሔዋን፣ የሚጀምር ሲሆን ከስሕተት በኋላም ይህች ቤተ ክርስቲያን (ምእመን) ዳግም የተፈጠረችው በሥላሴ እንደሆነ ጥናቱ ያትታል፡፡ በዚህ መሠረት ቤተ ክርስቲያን ክርስቶሳዊት ወይም መንፈስ ቅዱሳዊት ብቻ ናት የሚለውን ሐሳብ በመተቸት ቤተ ክርስቲያን ሥላሴያዊ መሠረትና የሕይወት ጉዞ እንዳላት ጥናቱ ይከራከራል፡፡ ይህ የቅዱስ ያሬድ ስለ ቅድስት ሥላሴያ የነገረ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ኦርቶዶክሳዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን ነገረ ቤተ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ በጥልቀት በመግለጥ ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ መለኮት ሊቃውንት ነገረ ቤተ ክርስቲያንን የመረዳት ብርሃን እንደሚፈነጥቅ ጥናቱ ያመለክታል፡፡