Post-Conflict Peace Building By The Inter-Religious Council Of Ethiopia (IRCE): The Case Of Agaro
Tsion Zeraykob
Abstract
ይህ የጥናት ወረቀት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም ግንባታ ጥረት ውስጥ ያለውን ሚና እና ተግባር ይተነትናል። በተጨማሪም፣ በምክር ቤቱ ላይ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች፣ ያሉትን ጥንካሬዎች፣ ምክር ቤቱ የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች እና የሰላም ግንባታ ጥረቱን ውጤታማነት ይገመግማል። የሠላም ግንባታ ጽንሰ ሐሳብ፣ በእምነት ላይ የተመሠረተ የሰላም ግንባታ ጽንሰ-ሐሳባዊ እና ንድፈ ሐሳባዊ ማዕቀፎቹ እና አሠራሮቹ ይብራራሉ። ለዚህም፣ ዓይነታዊ የጥናት ዘዴ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ለናሙና መረጣ የተመረጠው ዘዴ ነሲባዊ የናሙና ዘዴ በተለይም ወሳኝ የናሙና ዘዴ እና ስኖው ቦል ናቸው፡፡ የጥናቱ መረጃ የተሰበሰበው ለቁልፍ መረጃ ሰጪዎች ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ ቡድን ተኮር ውይይት በማድረግ እና ካልአይ መረጃ ዘዴዎችን በመጠቀም ነው፡፡ የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም ውይይቶች ጊዜ የአመቻችነት ሚና የነበረው ሲሆን ይህም በጅማ የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ብቸኛው የሰላም ግንባታ ዘዴ ነው። የተደረገው የሰላም ግንባታ ጥረትም ነባር አብሮ የመኖርን ዕሴት በከፊል ወደነበረበት መመለስ አስችሏል። የሃይማኖት መሪዎች ጥርጣሬ፣ የሕዝብ አመኔታ ማጣት፣ የገንዘብ ችግር እና ባህላዊ የግጭት አፈታት ቴክኒኮችን አለማካተት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ሆነው ቀርበዋል። ይሁን እንጂ፣ ከግጭት በኋላ የተካሄደው የሰላም ግንባታ መርሀ ግብር የሀገር ውስጥ ባለቤትነትን እና የሃይማኖት ተቋማትን ለግጭት አፈታት በማቀናጀት ከደረሰው ጉዳት አንፃር በአንጻራዊ ሁኔታ አብሮ መኖርን ያስገኘ በመሆኑ እንደ ጥንካሬ ተደርጎ ይወሰዳል። እንደማጠቃለያ፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው የሰላም ግንባታ ሂደት በትክክል ከተነደፈ እና ከተመራ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና መቻቻል እና ማኅበራዊ ትሥሥርን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።