መቅድም
Abstract
ምርምርና ሥርጸት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐዲስ ሥራ አይደለም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ በራሷ መንገድ እና አውድ ጥናት ታካሂዳለች። ቤተ ክርስቲያኒቱ በብራና ባህሏ አማካኝነት ለብዙ መቶ ዓመታት ዕውቀትን እያሰራጨች ትገኛለች። ከጊዜ ወደ ጊዜ የኅትመት ዓይነቶችና ዘዴዎች እየተሻሻሉ እና እየተለወጡ መጥተዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱም በዘመናዊው ዘዴ ዕውቀትን የሚያመርቱ እና የሚያሰራጩ ተቋማትን አቋቁማለች። ከእንዲህ ዓይነት ተቋማት አንዱ ከ30 ዓመታት በፊት የተቋቋመው ማኅበረ ቅዱሳን ነው። ማኅበረ ቅዱሳን በስፋት የሚሰራጩትን የሐመር መጽሔትን እና ስምዓ ጽድቅ ጋዜጣን ሲያሳትም ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪም የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ዘመናዊ የምርምር ኅትመቶች መድረክ ኾኖ እንዲያገለግል ከዐሥር ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔትን አቋቁሟል። ይህ ሰባተኛው የኢ.ቤ.ጥ.መ. ቅጽ ኅትመቱ ለአራት ዓመታት ከተቋረጠ በኋላ የወጣ ነው። የኢ.ቤ.ጥ.መ. አርትኦት ቦርድ ለተፈጠረው መቆራረጥ ይቅርታ እየጠየቀ የዚህ ቅጽ ኅትመት እውን እንዲኾን አስተዋጽዖ ላደረጉ ጽሑፍ አቅራቢዎች እና ገምጋሚዎች ምስጋናውን ያቀርባል። የአሁኑ የኢ.ቤ.ጥ.መ. እትም በዋናው ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱ ተዛማጅ ጽሑፎችን ለመጥቀስም ኾነ ዋቢ መጻሕፍትን ለማቅረብ የአሜሪካ ሥነ ባሕርይ ማኅበር (APA) 7ኛ እትም) ቅርጽን ተከትሏል። የኅትመት ቋንቋዎቹም ዐምስት፡ ማለትም ግእዝ፣ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ እና እንግሊዘኛ እንዲኾኑ በግልጽ አስቀምጧል። በዚህ ቅጽ ስድስት መጣጥፎች ቀርበዋል። አራቱ በአማርኛ ሲጻፉ ሁለቱ በእንግሊዘኛ የተጻፉ ናቸው። የመጀመሪያው መጣጥፍ የግእዝ ፊደል ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጻፊያነት መዋል እንደሚችል የመከራከሪያ ነጥቦችን ያቀርባል። ሁለተኛው ጽሑፍ ድጓ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ምእመናን ማኅበራዊ ሕይወት የሚጫወታቸውን ልዩ ልዩ ሚናዎች ያቀርባል። ሦስተኛው መጣጥፍ ስለ ታዋቂው የአንድምታ ትርጓሜ መምህርና የትርጓሜ ትምህርት ቤት መሥራች መምህር ኤስድሮስ ታሪክና የመሠረቱትን የአንድምታ ትምህርት ቤት በዝርዝር ያቀርባል። አራተኛው መጣጥፍ ስለ የበቆጂ ጨፋ መካነ ሕይወት መድኃኔ ዓለም ደብረ ቁስቋም አንድነት ገዳም መገደም መነሻ ትርክቶች ዝርዝር ጉዳዮችን ያቀርባል። ዐምስተኛው መጣጥፍ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐውድ ውስጥ ቁሳዊ ያልኾኑ ንብረቶችን ለመገመት የሚረዱ ዘዴዎችን ይዳስሳል። የመጨረሻው መጣጥፍ በኢትዮጵያ ያለውን ታሪካዊ የመንግሥት እና የሃይማኖት መስተጋብር ይገመግማል።