State- Religion Interactions in Ethiopia: Trajectories and Forms

Haileyesus Muluken

Abstract

ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ያለውን የመንግሥት እና የሃይማኖት መስተጋብር ተለዋዋጭነት አስመልክቶ አስቀድሞ የተዘጋጁ ሥነ-ጽሑፎችን በመገምገም ትንታኔ ይሰጣል። በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የመንግሥት እና የሃይማኖት መስተጋብሮች በሀገሪቱ ውስጥ ባለው የፖለቲካ እድገት፣ በሃይማኖት ቡድኖች ውስጥ እና በሃይማኖቶች መካከል ያለው የሥልጣን ሽግሽግ እና በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ ኹኔታዎች በሚወሰኑ ተደጋጋሚ ሂደታዊ ከፍታዎች እና ዝቅታዎች የሚታወቁ መኾናቸውን ጥናታዊ ግምገማው አመልክቷል። መስተጋብሮቹ ሊታዩ የሚችሉት በመጀመሪያ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን በመቀበል በሃይማኖት ጉዳይ ተቀራርቦ የመሥራት አካሄድን ተከትሎ፣ ቀጥሎም ወጥ የኾነ የቁጥጥር ተግባራት በማከናወን፣ ከዚያም በስውራዊ ተጽእኖ ውስጥ በማስገባት፣ በመጨረሻም ግልጽ በኾነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነው። መንግሥት በተከተላቸው በእነዚህ የመንግሥት የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት አቅጣጫዎች ውስጥ ደረጃዎች ያሉ ቢመስሉም፣ ያልተቋረጡ እና ተደጋጋሚ ባሕርያትም እንዲሁ ይስተዋሉባቸዋል። ይህ ጥናታዊ ወረቀት አስቀድመው የተዘጋጁት ሥነ-ጽሑፎች ሁሉም በሚባል ደረጃ ያሉባቸውን ተጨባጭ የጥናታዊ ሥነ ዘዴ ጥንካሬዎችን እና ድክመቶች ለይቶ አሳይቷል። ከጥናታዊ ሥነ ዘዴ አንጻር፣ ሁሉም ሥነ-ጽሑፎች ማለት በሚቻል ደረጃ ቁጥር ተኮር (quantitative) አቀራረብን ተከትለዋል። ይህ ቁጥር ተኮር ጥናታዊ ዘዴ ምሁራን የመንግሥት እና የሃይማኖት መስተጋብር ውስብስብ ተፈጥሮን እንዲለዩ የሚያስችል ቢኾንም፣ በተመሳሳይ ጊዜ ስለ ክሥተቶች አጠቃላይ ግንዛቤ እንዳይኖር ያደርጋል። ከአንዱ አውድ የተገኙ ውጤቶች ለሌሎች አውዶች ትርጉም ላይኖራቸው ይችላል፡፡ እንዲሁም የመንግሥት እና የሃይማኖት መስተጋብር ከቦታ ቦታ እና ከክልል ክልል ሊለያይ ይችላል። ከተጨባጭነት አንጻር ሲታዩ ደግሞ፣ በመንግሥትና በሃይማኖት ውጥረት ጊዜ ሥነ-ጽሑፎቹ በመንግሥትና በሃይማኖት መስተጋብር ላይ ጠንካራ ትንታኔ የሚሰጡ ቢኾኑም፣ የመንግሥትንና የሃይማኖትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና የዕለት ተዕለት ገጠመኞች ከመሸፈን አንጻር ግን ድክመት አለባቸው። ስለኾነም፣ በ ‘በሰላም ጊዜ’ የሚደረጉ በየእለቱ የሚኖሩ የመንግሥት እና የሃይማኖት መስተጋብሮች እንዲደበቁ ያደርጋሉ፡፡ ይህም፣ የመንግሥት እና የሃይማኖት መስተጋብር ተፈጥሮ እና ጥልቀት በውጥረት እና በሰላም ጊዜ ልዩነት ይኑረው አይኑረው የምናውቀው ነገር እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ከዚህም በላይ፣ ሥነ[1]ጽሑፎቹ የመንግሥትና የሃይማኖት መስተጋብርን በዋናነት በሁለቱ መካከል ያለውን ተቋማዊ ግንኙነት በኢሊቶቹ ላይ በማተኮር የማቅረብ አዝማሚያ አላቸው። የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ውጤት ደግሞ ምእመናን መንግሥትን እንዴት እንደሚመለከቱት እና በመንግሥት ርምጃ ምን ዓይነት ተጽእኖ እንደሚደርስባቸው የሚያሳይ አይኾንም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በግለሰብ አማኝ ደረጃ ያለውን አመለካከት መፈተሸ ወሳኝ ጉዳይ ነው ምክንያቱም የአክራሪነት መነሻዎች ተቋማዊ የመኾናቸውን ያህል ግለሰባዊ ክሥተቶችም ናቸውና ነው።

Downloads

Published

2022-07-23

How to Cite

State- Religion Interactions in Ethiopia: Trajectories and Forms: Haileyesus Muluken. (2022). Journal-of-Ethiopian-Church-Studies/የኢትዮጵያ-ቤተ-ክርስቲያን-ጥናት-መጽሔት-Live/, 7(7), 132–155. Retrieved from https://journals.eotcmk.org/index.php/files/article/view/46